የይዘት ማውጫ
ይህ ጽሁፍ መጨረሻ ላይ የታየው መጋቢት (March) 26 ቀን 2025 ነው።
አጭር መግለጫ
ይህ ጽሁፍ፤ በአስቸኳይ ከአገር የመባረር ሁኔታ ( expedited removal) ሲባል ምን ማለት እንደሆነና ይህ ሁኔታም ማንን እንደሚመለከት ያብራራል። የአሜሪካን መንግስት፤ ይህንን ሁኔታ በጥር ወር (January) 2025 እንዴት እንደሚያጠናክረው መረጃ ይሰጣል። ጽሁፉ ከወደታች የተዘረዘሩትን ያጠቃልላል፤
- በአስቸኳይ ከአገር ስለመባረር ሁኔታ (expedited removal) መረጃ መስጠት
- በዚህ ሂደት ውስጥ የሚመለከታቸው እነማን እንደሆኑ ማስረዳት
- በሂደቱ ውስጥ ሲገቡ ምን እንደሚከተል ማስረዳት እና
- በሂደቱ ውስጥ ከገቡ በኋላ አሜሪካን አገር ውስጥ ለመቆየት ከሁኔታው እንዴት መውጣት እንደሚቻል ማስረዳትን ያጠቃልላል።
በአስቸኳይ የመባረር ሁኔታ (expedited removal) ምን ማለት ነው?
በአስቸኳይ የመባረር ሁኔታ (Expedited removal ) ማለት የአሜሪካ መንግስት፤ የተወሰኑ ሰዎችን በአስቸኳይ ከአገር ለማስወጣት የሚያስችለው ሁኔታ ማለት ነው። ለምሳሌ ይህ በአስቸኳይ የመባረር ሁኔታ ለረጅም ግዜያት ሲሰራበት የቆየና ካለ ፈቃድ ወደ አገር የገቡና በጠረፉ ላይ ወይም ከጠረፉ በሚጠጋ ቦታ ላይ ከአሜሪካ የኢሚግሬሽን አባላት ጋር ግንኙነት ያደረጉ ሰዎችን በአስቸኳይ ከአገር እንዲባረሩ የማድረግ መብትን ለአሜሪካ መንግስት የሚሰጥ ነው።
በዚህ በአስቸኳይ የመባረር ሁኔታ (expedited removal) ዳኛ ፊት የመቅረብ መብት የለም። ሌላ የመንግስት ባለስልጣን፤ ጉዳዮን ፍርድ ቤት የማቅረብ መብት ሳይኖሮት ከአገር እንዲባረሩ ሊያዝ ይችላል። አንዴ ይህ ትእዛዝ ከተሰጠ በኋላ፤ ዜግነት ወደ አሎት አገር ሊባረሩ ይችላሉ። አንዳንዴም ወደ ሌላ አገር ሊባረሩ ይችላሉ።
ይህ ሂደት በትራምፕ አስተዳደር እንደተቀየረ ሰምቻለሁ። በዚህ አስቸኳይ የመባረር ሁኔታ ውስጥ ያሉት አዲስ መመርያዎች ምንድናቸው? በእኔ ላይ ተጽእኖ የሚያደርጉ መሆናቸውን እንዴት ነው ማወቅ የምችለው?
የአሜሪካ መንግስት፤ የመግብያ ቪዛ (ፈቃድ) ሳይኖራቸው ወደ አሜሪካን አገር የገቡና አሜሪካን አገር ውስጥ ከሁለት ዓመታት በላይ መቀመጣቸውን ማረጋገጥ የማይችሉ ሰዎች ከጥር (January) 23 ቀን 2025 ጀምሮ በዚህ አስቸኳይ ከአገር የማባረር ሁኔታ (expedited removal) ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ ይላል። በአሜሪካን አገር ህጋዊ መግብያ በሮች ላይ የደረሱና ወደ አሜሪካን አገር እንዲገቡ ፈቃድ የሚጠይቁ ሁሉም በዚህ በአስቸኳይ የመባረር ሁኔታ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ።
የመግብያ ቪዛ ሳይኖራቸው ወደ አሜሪካን አገር የገቡ ወይም ሌላ ህጋዊ የሆነ የመግብያ ፈቃድ ሳይዙ በእነዚህ ሁለት ዓመታት ውስጥ አሜሪካን አገር የገቡ ሰዎች በዚህ የአስቸኳይ የመባረር ሁኔታ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። የአሜሪካን መንግስት፤ ከጥር (January) 23 ቀን 2025 ጀምሮ፤ ወደ አሜሪካን አገር ሲገቡ ከእስር የመለቀቅ ታሪክ ያላቸውን ሰዎችንም ሳይቀር በዚህ የአስቸኳይ የመባረር ሁኔታ ውስጥ ሊያስገባቸው ይችላል። እኛ እንደተረዳነው ከሆነ፤ የአሜሪካን መንግስት፤ የአሜሪካ የኢሚግሬሽን አባላት በአሁኑ ግዜ ከእስር ተለቀው ወደ አሜሪካን አገር በአንዳች ፕሮግራም የገቡትን ሰዎች ጉዳይ እያጤኑ በዚህ የአስቸኳይ የመባረር ሁኔታ ውስጥ የሚገቡ መሆናቸውንና አለመሆናቸውን እንዲያጣሩ ጠይቋል።
የአሜሪካ መንግስት፤ ይህ ህግ ወይም ይህ በአስቸኳይ የመባረር ሁኔታ፤ በድንበር የጸጥታ ጥበቃ በ ሲ-ቢ-ፒ (CBP) ቀጠሮ ተይዞላቸው ወደ አሜሪካ የገቡ ሰዎችንና ከእስር የተለቀቁ የኩባ፣ የሄቲ፣ የኒካራጉዋ ወይም የቬኑዜላ ተወላጆችን ይመለከታል። ሌሎችንም ሰዎች ሊመለከት ይችላል።
ጥገኛነት እንዲሰጣቸው ጉዳያቸው ወደ ኢሚግሬሽን ፍርድ ቤት የቀረበ ሰዎች፤ የአሜሪካን መንግስት ጉዳያቸውን ለመሰረዝና እነሱንም በዚህ በአስቸኳይ ከአገር የመባረር ሁኔታ ውስጥ እንዲገቡ ለማድረግ ይሞክር ይሆናል። መንግስት ይህንን ፖሊሲ ወይም መመርያ ከአንድ ወይም ከሁለት ዓመታት በፊት ወደ አሜሪካ በገቡ ከእስር በተለቀቁና እስከአሁን ጥገኛነት እንዲሰጣቸው ባላመለከቱ ሰዎች ላይ ጭምርም ሊጠቀምበት እንደሚፈልግ ይገልጻል።
መንግስት፤ መጋቢት (March) 2025 ላይ፤ ሌሎች ዝርዝሮችንም ሰጥቷል። በተለይም መንግስት በሰጠው አዲስ መመርያ፤ የኢሚግሬሽን አባላት የአይስ (አይ-ስ-ኢ-ICE) ማጣርያ ስራ በሚያደርጉበት ግዜ፤ በተለይ የጥገኝነት ወይም የስደተኛነት ማመልከቻ ያላስገቡ የሚከተሉት ዓይነት ቡድኖችን ወይም በፍርድ ቤት እንዲባረሩ የተፈረደባቸውን ሰዎች በዚህ የአስቸኳይ የመባረር ሁኔታ ውስጥ ሊያስገቧቸው እንደሚችሉ ተናግሯል:
- ካለአንዳች ፈቃድ ወደ አሜሪካን አገር የገቡ ግን ድንበር ላይ፤ ወደ አሜሪካን አገር የገቡበት ግዜ ግምት ውስጥ ሳይገባ፤ በኢሚግሬሽን ባለስልጣናት ወደ አሜሪካን አገር እንዲገቡ የተደረጉ ሰዎች
- “ከቅድመ-ሁኔታዎች ጋር መለቀቅ” (parole with conditions) ወይም “መለቀቅ ከእንደገና መታሰር አማራጭ ጋር” (parole + alternatives to detention) በሚል ወደ አሜሪካን አገር የገቡ
- ገና ድንበር ላይ እያሉ “ሪፖርት የማድረግ ትእዛዝ” በኢሚግሬሽን ፖሊሶች የተሰጣቸው ሰዎች።
በአስቸኳይ የመባረር ሁኔታ (expedited removal) ውስጥ ከገቡና ጉዳዮ በፍርድ ቤት እንዲታይ የተደረገ ከሆነ፤ በኦቶማቲክ መንገድ በፔሮል (parole ) ላይ መሆኖ ይቋረጣል።
የተቀየረው ምንድነው? እነኚህ ለውጦች ለምንድነው አስፈላጊ የሆኑት?
ከእነዚህ ለውጦች በፊት፤ አሜሪካን አገር ውስጥ ያሉ ሰዎች፤ ከድንበሩ በ 100 ማይልስ ርቀት ላይ ከሆኑና ወደ አሜሪካ ከገቡ በ 14 ቀናት ውስጥ በአሜሪካ መንግስት ከተያዙ፤ በዚህ በአስቸኳይ የመባረር ፕሮግራም ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ።
በአሁኑ ግዜ ደግሞ፤ ወደ አሜሪካን አገር የገቡት ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ከሆነና ወደ አሜሪካን አገር የገቡት ካለ ቪዛ ወይም ሌላ ዓይነት የመግብያ ፈቃድ ከሆነ ወይም ከላይ በተጠቀሱት ቡድኖች ውስጥ ከሆኑ በአስቸኳይ የመባረር ሁኔታ ውስጥ እንዲገቡ ሊደረጉ ይችላሉ። ከድንበሩ ምን ያህል ርቀው ላይ እንደሚገኙ አስፈላጊነት የለውም። ይህም ማለት በጣም ቁጥራቸው ብዙ የሆኑ ሰዎች በዚህ በአስቸኳይ የመባረር ሁኔታ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ ማለት ነው።
ስለዚሁ በአስቸኳይ የመባረር ሁኔታ የሚነሱ የተለመዱ ጥያቄዎች
በዚህ በአስቸኳይ የመባረር ሁኔታ ውስጥ እንድገባ ከተደረኩ፤ አሜሪካን አገር ውስጥ ለመቆየት ጥገኛነት ወይም ሌላ ዓይነት ፈቃድ ለመጠየቅ እችላለሁን?
በዚህ በአስቸኳይ የመባረር ሁኔታ (expedited removal) ውስጥ ከገቡ በኋላ ጥገኝነት ለማግኘትም ሆነ አሜሪካን አገር ውስጥ ለመቆየት የሚያስችል መንገድ እንዳለ ለማወቅ የሚችሉት ማመልከቻ ካስገቡ በኋላ ነው። በዚህ በአስቸኳይ የመባረር ሁኔታ (expedited removal) ውስጥ ከገቡ በኋላ ጥገኝነት ለማግኘት ማመልከት ይችላሉ ብሎ የአሜሪካ መንግስት ራሱ ካልወሰነ በስተቀር፤ የጥገኝነት ማመልከቻ ማስገባት አይቻልም።
ጥገኝነት እንዲሰጠኝ ማመልከቻ ማስገባት እንድችል እንዴት ነው የአሜሪካን መንግስትን መጠየቅ የምችለው?
ወደ አገሮ መመለስ የሚፈሩና ይህንን ፍርሃትዎን ለአሜሪካ መንግስት ባለስልጣን የገለጹ ከሆነ፤ ቃለመጠይቅ እንዲያደርጉ ይጠየቃሉ። በዛ ቃለመጠይቅ የሚናገሩት፤ የአሜሪካን መንግስት፡ የጥገኛነት ማመልከቻ እንዲያስገቡ ወይም ሌላ በአሜሪካን አገር የሚያስቆይ ፈቃድ እንዲሰጦት ለመወሰን ያግዘዋል።
ይሁንና ማስታወስ የሚገባዎት ነገር ካለ የኢሚግሬሽን ባለስልጣኖች ወደ አገሮ መመለስ ያስፈራዎታልን፤ የጥገኛነት መብት እንዲሰጦት ማመልከቻ ማስገባት ይፈልጋሉን ብለው ራሳቸው እንደማይጠይቆት ነው። ይህም ማለት እንዳዛ ብለው ጭራሽ አይጠይቁዎትም ይሆናል ማለት ነው። በዚህም ምክንያት፤ ወደ አገሮ መመለስ የሚፈሩ ከሆነ፤ ይህንን ለአሜሪካ ባለስልጣናት በተቻለ መጠን በፍጥነትና በተደጋጋሚ ማስረዳት አለቦት። ከአንድ ሰው በላይ ለብዙ ሰዎች መናገር አለቦት። አንዴም ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ መናገር አለቦት።
ሌላ ማወቅ ያለቦት ደግሞ ከቤተሰብዎ ጋር ከሆነ ያሉት፤ ከእነሱ ሊለያዩ እንደሚችሉ ነው። ስለዚህ ወደ አገሮ ለመመለስ ፍርሃት ወይም ስጋት ካሎት፤ እያንዳንዱ የቤተሰብዎ አባል ይህንን ማወቅና እነሱም ወደ አገር የመመለስ ፍርሃት ለምን እንዳለባቸው ለሁሉም የኢሚግሬሽን አባላት በተደጋጋሚና በፍጥነት መናገር እንዳለባቸው ማረጋገጥ ይኖርቦታል። ይህ ልጆችንም ይመለከታል።
የቃለመጠይቁ ሂደት ምን ይመስላል?
እርሶ ወደ አገሮ ለመመለስ ከፍተኛ ፍርሃት እንዳለቦት ለአንድ የኢሚግሬሽን አባል ከገለጹ፤ ቃለመጠይቅ እንዲያደርጉ ይጠየቃሉ። የግል ሁኔታዎ ምን እንደሚመስል ግምት ውስጥ በማስገባት የሚደረግሎት ቃለመጠይቅ ‘ሃቀኛ/አስተማማኝ ፍርሃት (credible fear interview) እንዳለ የሚያረጋግጥ ቃለመጠይቅ ወይም ምክንያታዊ የሆነ ፍርሃት (reasonable fear interview) እንዳለ የሚያረጋግጥ ቃለመጠይቅ በመባል ይታወቃል። እዚህ ላይ ስለ ቃለመጠይቁ መታወቅ ያለበት ዋናው ቁም ነገር፤ የኢሚግሬሽኑ ባለስልጣን ይህንን ቃለመጠይቅ የሚያደርግሎት፤ ወደ አገሮ ለመመለስ ለምን እንደሚፈሩ ምክንያቱን ለማወቅና በዚህም ምክንያት በአገር ውስጥ ለመቆየት ማመልከቻ ለማስገባት መቻሎንና አለመቻሎን ለማረጋገጥ ብቻ ነው። ከኢሚግሬሽን ባለስልጣን ጋር በሚደረግ ማንኛውም ቃለመጠይቅ እውነት መናገር በጣም አስፈላጊ ነው።
አስታውሱ፤ ይህ ቃለመጠይቅ ስላደረጉ የጥገኝነት መብት ይሰጦታል ማለት አይደለም። ቃለመጠይቁን በተሳካ መንገድ ካለፉ የጥገኝነት መብት ለማግኘት ማመልከቻ እንድታስገቡ የመፍቀድ ዕድል ብቻ ነው የሚሰጦት።
ስለዚህ የቃለመጠይቅ ጉዳይ ተጨማሪ መረጃ ከፈለጉ ይህንን ይጫኑ።
ከሚደርስ ስቃይ መከላከል (Convention Against Torture) የተሰኘ ቃለመጠይቅ እንዲያደርጉም ሊጠየቁ ይችላሉ። በዚህ ቃለመጠይቅ፤ ቀደም ሲል ስለደረሰቦት ስቃይ ወይም ወደ አገሮ ከተመለሱ ሊያጋጥሞት ስለሚችል ስቃይ እንዲገልጹ ይጠየቃሉ።
በዚህ በአስቸኳይ ከአገር የመባረር ፕሮግራም ውስጥ እንድገባ ከተደረገ ልታሰር እችላለሁን?
አዎን። ሊታሰሩ ይችላሉ። ይህም እንደሚሆን በአብዛኛው የተረጋገጠ ነው። በዚህ በአስቸኳይ ከአገር መባረር ሁኔታ ውስጥ የገቡ አብዛኛዎቹ ሰዎች፤ የአሜሪካ ባለስልጣናት የመባረሩን ሁኔታ ውጣ ውረድ እስኪያዘጋጁ ድረስና ቃለመጠየቁም በሚደረግበት ወቅት በ እስር ላይ ናቸው። እዚህ ላይ እስራት ማለት በእስር ቆይታ (custody) ውስጥ መሆን ማለት ነው።
በዚህ በአስቸኳይ የመባረር ሂደት ውስጥ እያለሁ ጠበቃ ላደርግ እችላለሁን?
አዎን። ጠበቃ ሊያደርጉ ይችላሉ። አስቸኳይ የመባረር ሁኔታ እውነትም በአስቸኳይ የሚደረግ ስለሆነ፤ ወድያዉኑ ጠበቃ ጋር መነጋገር እጅግ አስፈላጊ ነው።
በእስር ውስጥ ሲገቡ፤ ጠበቃ የማድረግም ሆነ ጠበቃ ለማግኘት ስልክ የመደወል መብት አሎት። (ይህም ማለት ማንም ባለስልጣን ጠበቃ የመያዝም ሆነ ጠበቃ ለመፈለግ የሚደረግ የስልክ ጥሪ እንዳያደርጉ የመከልከል መብት የለውም ማለት ነው)።
ምንም ያልገባዎት ዶኩመንቶች ላይ ያለመፈረም በጣም አስፈላጊ ነው። እርሶ ወይም እርሶ የሚያውቁት ሰው በዚህ በአስችኳይ የመባረር ሁኔታ ውስጥ የመግባት አደጋ ካለ፤ ከህግ አስከባሪ ሰዎች ጋር ከመነጋገሮ በፊት ጠበቃ ጋር መመካከር እጅግ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።
ከዚህ ከአስቸኳይ የመባረር ሁኔታ እንዴት ነው መውጣት የምችለው? ዳኛ ፊት መቅረብ እችላለሁን?
ያንን ምክንያታዊ ወይም አስተማማኝ የፍርሃት ሁኔታ በመባል የተደረገሎትን ቃለመጠይቅ ካለፉ፤ የኢሚግሬሽን ፍርድ ቤት ውስጥ እንዲቀርቡ ይደረጋል። ይህም ማለት ጉዳዮን ወደ ኢሚግሬሽን ዳኛ ለማቅረብ ዕድል ያገኛሉ ማለት ነው። ወደ አገሮ ቢመለሱ ምክንያታዊ ወይም አስተማማኝ የሆነ ስቃይ እንደሚደርስቦት ያሎትን ፍራቻ በግልጽ ለዳኛው ካላስረዱ ወይም ባደረጉት የፍርሃት ቃለመጠይቅ አዎንታዊ ውሳኔ ካላገኙ፤ የአሜሪካ ኢሚግሬሽን ባለስልጣናት፤ ገና ዳኛ ፊት ከመቅረቦ በፊት፤ በፍጥነት ወይም በአስቸኳይ ከአገር እንዲባረሩ ሊያደርጉ ይችላሉ። ከዚሁ ከአስቸኳይ የመባረር ሁኔታ ወጥተው ወደ ኢሚግሬሽን ፍርድ ቤት ቢሻገሩም ጉዳዮ በአጠቃላይ እስኪዘጋ ድረስ በእስር ይቆያሉ።
በዚህ በአስቸኳይ የመባረር ሁኔታ እጅግ የምጨነቅ ከሆነ ምን ማድረግ አለብኝ?
በአሜሪካን አገር የመኖር ህጋዊና ቋሚ የፍቃድ ወረቀት የሌለውና ወደ አሜሪካን አገር በእነዚህ ሁለት ዓመታት ውስጥወደ አሜሪካን አገር የገባ ሰው የሚቻል ከሆነ፤ ይህንን የግል ጉዳዮን አስመልክቶ ከጠበቃ ጋር ይወያይ። የኢሚግሬሽን ጠበቃ፤ ጉዳዮን በተመለከተ አሜሪካን አገር ውስጥ ለመቆየት ጥገኝነት መጠየቅ ወይም ሌሎች በአገር ውስጥ የሚያስቆዮት ዘዴዎች እንዳሉ ማመልከት ይሻል መሆኑና አለመሆኑም በመምከር ሊያግዞት ይችላል። እኛ፤ የአሜሪካ ኢሚግሬሽን ባለስልጣናት፤ እነኚህን አዲስ ፖሊሲዎች እንዴት በተግባር ሊተርጉሙ እንደሚችሉ በትክክል የምናውቀው ነገር የለም።
በዚህ በአስቸኳይ የመባረር ፕሮግራም እጅግ የሚጨነቁ ከሆነና ምናልባት የህግ አስፈጻሚዎች መንገድ ላይ ካስቆሞት፤ ዘወትር ከእርሶ ጋር ይዘዋቸው መዞር ያለቦት ነገሮች አሉ። እነሱም፡
-
በአሜሪካን አገር የመኖር ህጋዊ ፍቃድ ያሎት ከሆነ፡
- ህጋዊ የሆነ ወረቀትዎን ለምሳሌ የኢሚግሬሽን ወይም የዜግነት ወረቀቶችዎን
-
ገና በፍርድ ቤት በመታየት ላይ ያለ የጉዳዮን ሂደት የሚያሳይ ወረቀት ወይም ማመልከቻ:
- ገና በመታየት ላይ ያለ ጉዳይ ወይም ማመልከቻ በተለይም ጥገኝነት ለማግኘት ያስገቡት ማመልከቻ እንዳሎት የሚያሳዩ ወረቀቶች። የሚያሳዝነው ግን ይህ ሁሉ ወረቀት እያሎትም መንግስት በዚህ በአስቸኳይ የመባረር ሁኔታ ውስጥ ሊያስገባዎት ሊሞክር ይችላል።
-
ወደ አገር ውስጥ ከገቡ ከሁለት ዓመታት በላይ ከሆነ፡
- በአሜሪካን አገር ምን ያህል ዓመታት እንደቆዩ የሚያሳይ ወረቀት፤ ይህም የአየር ቲኬት፣ የመንግስት መታወቅያ ወረቀት፣ መጻህፍት ከቤተ መጻህፍት የሚያወጡበት ካርድ፣ ስምዎ፣ አድራሻዎና ወደ እርሶ የተላከበት ቀን ያለበት ፖስታ፣ የት/ቤት መዛግብት፣ የቤት ኪራይ ውል ወረቀትና አሜሪካን አገር ውስጥ ከሁለት ዓመታት በላይ እንደኖሩ የሚያሳዩ ሌሎች ተመሳሳይ ወረቀቶችን ሊያጠቃልል ይችላል።
አስታውሱ፡ ስለ ኢሚግሬሽን ሁኔታዎ ማንኛውንም ጥያቄ ለመመለስ አይገደዱም። በኢሚግሬሽን አባላት ሲጠየቁ ስላሎት መብቶች ተጨማሪ መረጃ ካስፈለጎት እዚህ ላይ ይጫኑ።
ተጨማሪ መረጃዎችና ምንጮች
የኤን-አይ-ኤል-ሲ (NILC) የአስቸኳይ የመባረር ሁኔታ ማጠናከርያ(Expedited Removal Expansion) በተመለከተ ያሎትን መብቶች ይወቁ
Comments
0 comments
Please sign in to leave a comment.