የይዘት ማውጫ
ይህ ጽሁፍ መጨረሻ የተሻሻለው ሐምሌ ( July) 14 ቀን 2026 ነው።
አጭር መግለጫ
የአሜሪካ ዜጎች (ዩ ኤስ ሲ ኤስ USCs) እና በአሜሪካን አገር ህጋዊና ቋሚ ኗሪዎች የሆኑ ሰዎች ኤል ፒ አር(LPRs) ወይም ግሪን ካርድ (green card) ያላቸው ሰዎች፤ ፎርም I-130 (Form I-130) የተባለ የጥያቄ ማቅረብያ ፎርም በመሙላት ከአገር ውጪ ያሉትን የተወሰኑ ዘመዶቻቸውን ወደ አሜሪካ እንዲመጡ ማገዝ ይችላሉ። ይህም በተጨማሪ “በቤተሰብ ላይ የተመረኮዘ ኢሚግሬሽን” ተብሎ ይጠራል።
ይህ ጽሁፍ ዘመድ ለማስመጣት ፎርም I-130 ለማስገባት ለሚፈልጉ የአሜሪካ ዜጎችና ቋሚና ህጋዊ የመኖርያ ወረቀት ላላቸው ሰዎች መመርያ የሚሰጥ ነው። ስደተኛ (refugee) ወይም ጥገኝነት የተሰጦት ሰው (asylee) ከሆኑ ለሁለቱም ለስደተኛና ጥገኝነት ለተሰጠ ሰው የሚሰጥ ቤተሰብ የማስመጣት ዕድል ብቁ ሊሆኑ ይችላሉ። እነኚህን አማራጮች በተመለከተ መረጃ ከፈለጉ እዚህ ይመልከቱ።
የጉዞ እገዳ ዝማኔ
ምንም እንኳን ከታች በተዘረዘረው መሰረት ቪዛ ለማግኘት የተፈቀደላቸው ቢሆኑም በአሁኑ ግዜ ወደ አሜሪካን አገር ለመግባት ለሚፈልጉ አንዳንድ ሰዎች አያሌ የጉዞ እገዳዎች አሉ። ይህ እገዳ በኢሚግሬሽን ሂደት ውስጥ በመጀመርያው ደረጃ ላይ ያሉትን ሰዎች የማይነካ ሊሆን ይችላል ግን በሂደቱ ከፍ ወዳለ ደረጃ በደረሱ አመልካቾች ላይ ተጽእኖ ሊያደርግ ይችላል። እዚህ በ2025 ስለተደረገው የጉዞ እገዳና በ2026 ስለቆመው የስደተኞች ቪዛ ተጨማሪ መረጃ ከፈልጉ ይመልከቱ።
በቤተሰብ ላይ የተመረኮዘ የኢሚግሬሽን ሂደት ምን ማለት ነው?
የዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ (USCIS) ማመልከቻ
የዚህ ሂደት የመጀመርያው እርምጃ፤ ፎርም I-130(Form I-130) ሞልቶ ወደ የአሜሪካ የዜግነትና የኢሚግሬሽን አገልግሎት ዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ (U.S. Citizenship and Immigration Services (USCIS) መላክ ነው። ይህም የዘመድ ጥያቄ ማቅረብ (petitioning) ተብሎ ይጠራል። እርሶ ጥያቄ አቅራቢ (petitioner) ኖት። ከዚህ ጥያቄዎ ጋር አብሮ የአሜሪካ ዜጋ ወይም ግሪን ካርድ (green card) ያዥ መሆንዎን የሚያስረዳ ዶኩመንት ማቅረብ አለቦት ። ወደ አሜሪካን አገር መምጣት የሚፈልገው ሰው ደግሞ ከእርሶ ጋር እንዴት እንደሚዛመድ የሚያስረዳ ማረጋገጫ ማቅረብ አለቦት ። ይህ ሰውም ተጠቃሚ (beneficiary) ይባላል።
ፎርሙን በሚሞሉበት ወቅት፤ ለጥያቄ አቅራቢው ማለትም ለእርሶ የሚቀርቡትን ጥያቄዎች በሙሉ፤ ስለራስዎ መረጃ በመስጠት መመለስ አለቦት።
ቋሚ የመኖርያ ፈቃድ ለማግኘት የሚደረግ ማመልከቻ
የሞሉትና ያስገቡት የ I-130 ማመልከቻ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ፤ ዘመድዎ ቋሚ የአሜሪካን አገር የመኖርያ ፈቃድ ለማግኘት ማመልከት አለበት ።
ዘመዶ የሚኖረው ከአሜሪካን አገር ውጪ ከሆነ፤ ይህንን ቆንስላዊ ሂደት (consular processing) በተባለ አገባብ ያደርጋል። ይህም ማለት የስደተኛ ቪዛ ለማግኘት ባለበት አገር ባለው የአሜሪክ ኤምባሲ ወይም ቆንስል በኩል ያመለክታል ማለት ነው። የቪዛ አመልካች ተብሎም ይጠራል።
ይሄው ዘመዶ ያለው በአሜሪካን አገር ውስጥ ከሆነ፤ የሁኔታ መስተካከል (“adjustment of status) የሚባል ፎርም በመሙላት ግሪን ካርድ(green card) ለማግኘት ማመልክት ያስፈልገው ይሆናል ። በዚህም የመስተካከል አመልካች ተብሎ ይጠራል።
ይህ መመርያ የዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ (USCIS) ጥያቄ ሂደትን ብቻ የሚያስረዳ ነው።
እንዲመጡ ለመጠይቅ የምችለው ለእነማን ነው?
ህጋዊና ቋሚ ወረቀት ያሎት (ኤል ፒ አር LPR) ከሆነ፤ ባለቤትዎ ወይም በማንኛውም ዕድሜ ላይ የሚገኙ ያላገቡ ልጆችዎ እንዲመጡ መጠየቅ ይችላሉ።
የአሜሪካ ዜጋ (ዩ ኤስ ሲ USC) ከሆኑ፤ ባለቤትዎ ወይም በማንኛውም ዕድሜ ላይ የሚገኙ (ያገቡም ሆኑ ያላገቡ) ልጆችዎ እንዲመጡ መጠየቅ ይችላሉ።ዕድሜዎ ከ21 ዓመት በላይ ከሆነ፤ ወላጆችዎንና እህትና ወንድሞን ለማስመጣት መጠየቅ ይችላሉ።
የት ነው የምጀምረው?
እዚህ የሚገኘውን ፎርም I-130 (Form I-130) መሙላት አለቦት ። ይህንን ፎርም I-130 ከሞሉ በኋላ በሁለት ዓይነት መንገድ መላክ ይችላሉ፤1) በፖስታ ወይም 2) በዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ ( USCIS) ዊብሳይት በኦንላይን። ስለሁለቱ አማራጮች የበለጠ መረጃ እዚህ ያገኛሉ።
የአሜሪካ ቋሚ ተቀማጭ ኤል ፒ አር ( LPR) ከሆኑ፡ ለዘመድዎ አንድ የጥያቄ ፎርም ብቻ ነው ሞልተው ማስገባት ያለቦት። ዕድሜያቸው ከ 21 ዓመት በታች የሆኑ ያላገቡ ልጆች ካሉት ሌላ የተለየ ማመልከቻ ፎርም መሙላት አያስፈልጎትም። ይሁንና የሚያቀርቡት ጥያቄ ባለቤትዎና ልጆችዎ እንዲመጡሎትና ጉዳያቸው ለየብቻ እንዲታይሎት የሚፈልጉ ከሆነ ለእያንዳንዱ ሰው የተለየ ማመልከቻ ማስገባት ይችላሉ።
የአሜሪካ ዜጋ ዩ ኤስ ሲ ( USC) ከሆኑ፡ ለዓቅመ አዳም ለደረሱና ላገቡ ልጆችዎ ወይም እህት ወንድሞ ከሆነ ለማስመጣት ማመልከቻ የሚያስገቡት፤ ለባለቤቶቻቸውና ዕድሜያቸው ከ 21 ዓመት በታች ለሆኑ ልጆቻቸው የተለየ ማመልከቻ መሙላት የለቦትም።
የአሜርካ ዜጋ ዩ ኤስ ሲ ( USC) ከሆኑና፣ ማመልከት የሚፈልጉት ለወላጆቾና ዕድሜያቸው ከ 21 ዓመት በታች ለሆኑ ልጆቻቸው ወይም ባለቤት ከሆነ፣ ለእያንዳንዱ ግለሰብ የራሱ የሆነ ማመልከቻ ማስገባት አለቦት።
የምትልኳቸውን ዶኩመንቶች ዝርዝር በልዩ ወረቀት ጽፈው አብረው መላክ አለቦት። ይህም ዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ (USCIS) የተጠየቁትን ዶኩመንቶች በሙሉ መላኮን ለማየት ያግዘዋል።
ፎርሙን በፖስታ ሲልኩ፤ በእጅዎ ከተፈርመ ፊርማዎ ወይም ስካን (scan) ከተደረገ ፊርማዎ ወይም በእጅ የፈረሙት ፊርማ ቅጂ ጋር መሆን አለበት። ዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ (USCIS) ታይፕ የተደርገ ወይም የኢሌክትሮኒክ ፊርማ አይቀበልም። ወደ ዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ (USCIS) ስካን (scan) የተደረገ ፊርማዎ ወይም በእጅ የፈረሙት ፊርማ ቅጂ ከላኩ፤ ኦሪጂናል ፊርማዎን ማቀብ አለቦት ምክን ያቱም ወደፊት እንደገና ለዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ (USCIS) ማሳየት ያስፈልጎት ይሆናል።
ዘመዴን ለማስመጣት የሚከፈለው የማመልከቻ ክፍያ ምን ያህል ነው?
ለ I-130 ማመልከቻ ፎርም የሚከፈል ክፍያ አለ። ከግንቦት (May) 2025 ወዲህ፤ ማመልከቻዎን የሚያስገቡት በፖስታ ነው ወይስ በኤሌክትሪካዊ መንገድ ግምት ውስጥ ገብቶ የተለያዩ ክፍያዎች አሉ። የ I-130 ፎርሙን በፖስታ ከላኩ፤ የሚከፍሉት ገንዘብ $675.00 ነው። የ I-130 ፎርሙን በኦንላይን ከሆነ የሚልኩት የሚከፍሉት $625.00 ነው።
በፖስታ ለሚላኩት ማመልከቻዎች፤ በክሬዲት ካርድ (credit)፣ በዴቢት (debit) ካርድ ወይም አስቀድሞ በሚከፈል (prepaid) ካርድ መከፈል ይቻላል፤ ከክፍያዎም ጋር እዚህ የሚገኘውን ፎርም Form G-1450 ሞልተው አብሮ መላክ አለቦት። እዚህ የሚያገኙውን ፎርም Form G-1650 በመሙላትም ከባንክ ሂሳቦ በቀጥታ የሚከፈል ማድረግ ይችላሉ። ነጻ የሚያደርጎት ነገር (exemption) ከሌለ በስተቀረ፤ ጥሬ ገንዘብ መክፈል አይቻልም፤ በቼክ ወይም በገንዘብ ትእዛዝ ( money order) መክፈልም ቀርቷል። የሚከፈለው ገንዘብ እንዴት እንደሚከፈል ሊቀያየር ይችላል። በመሆኑም ማመልከቻዎን ከማስገባትዎ በፊት ይህንን ወደ ዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ ዌብሳይት በመግባት ያጣሩ።
ማመልከቻዎን በኦንላይን ከሆነ የሚልኩት፤ የ ዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ ዌብሳይት ስርዓት፤ ክፍያዎን የሚያደርጉት የዴቢት፣ የክሬዲት ወይም አስቀድሞ የሚከፈል ካርድ ሂደት እንዴት እንደሚደረግ ይመራዎታል። ክፍያዎን በኦንላይን ለመክፈል፤ ስርዓቱ በኦቶማቲክ መንገድ ደህንነቱ ወደ ተጠበቀ ቦታ፣ ፔ ዳት ጋቨ (pay.gov) ይመራዎታል። በኦንላይን ለሚላክና በኦንላይን ለሚደረግ ክፍያ ተጨማሪ መረጃ ከፈልጉ እዚህ ይመልከቱ።
ከI-130 ማመልከቻ ጋር ሌላ መላክ ያለብኝ ምን አለ?
በቅድሚያ፡ የአሜሪካን ዜጋ (ዩ ኢስ ሲ USC) ወይም ህጋዊና ቋሚ ተቀማጭ (ኤል ፒ አር LPR) መሆንዎን ማረጋገጥ አለቦት።
የ I-130 ፎርም፤ እርሶን ጥያቄ አቅራቢውን (petitioner) በአሜሪካን አገር ያሎትን የመኖርያ ወረቀት ለማረጋገጥ ዶኩመንቶችን ላኩ ብሎ ይጠይቆታል።
የአሜሪካን ዜጋ (ዩ ኤስ ሲ USC) መሆንዎን ለማረጋገጥ፣ ከእነዚህ ከታች ከሰፈሩት ዶኩመንቶች ውስጥ አንዱን ከ I-130 ፎርም ጋር መላክ አለቦት ።
- አሜሪካን አገር እንደተወለዱ የሚያሳይ የልደት የምስክር ወረቀት ቅጂ
- ዜጋ የሆኑበት(naturalization) የምስክር ወረቀት ቅጂ
- የዜግነት የምስክር ወረቀት ቅጂ
- በውጭ አገር እንደተወለዱ የሚያሳይ በውጭ የመወለድ ቆንስላዊ ሪፖርት Consular Report of Birth Abroad (ሲ አር ቢ ኤ (CRBA)ቅጂ
- ያልተቃጠለ የአሜሪካን ፓስፖርትዎ ቅጂ ወይም
- በአሜሪካ ቆንስል ጽህፈት ቤት ባለስልጣን፤ ደንበኛ ፓስፖርት ያሎት የአሜሪካ ዜጋ መሆንዎን በማረጋገጥ የተጻፈ ደብዳቤ
የአሜሪካን አገር ህጋዊና ቋሚ ተቀማጭ ኤል ፒ አር ( LPR) መሆንዎን ለማረጋገጥ፤ የግሪን ካርዶን (Green Card) የፊትና የኋላ ገጽን ፎቶ አስነስተው ቅጂውን መላክ አለቦት።
ግሪን ካርዶን ገና ያላገኙ ከሆነ፤ ፎቶዎ ያለበት ገጽና ወደ አሜሪካን አገር እንደ ህጋዊ መኖርያ ያለው ሰው የገቡበት ቀን የሚያሳይ ገጽ ጨምረው የፓስፖርቶን ቅጂ መላክ ይችላሉ። በተጨማሪም የ I-94 ቅጂዎን መላክ ይችላሉ።
ሁለተኛ፡ ከዘመድዎ ጋር ያሎትን ዝምድና ማረጋገጥ መቻል አለቦት።
የ I-130 ፎርሙ እርስዎን ጥያቄ አቅራቢውን (petitioner)፤ ከተጠቃሚው (beneficiary)ሰው ጋር ያሎትን የቤተሰብ ግንኙነት የሚያረጋግጡ ዶኩመንቶችን መላክ አለቦት ። ወደ ዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ (USCIS) ኦሪጂናል ወይም ዋና ዶኩመንቶችዎን አይላኩ። ሁሌም ቢሆን መላክ ያለቦት ቅጂዎችን ነው።
ዶኩመንቶቹ የተጻፉት በእንግሊዘኛ ቋንቋ ካልሆነ፤ ወደ እንግሊዘኛ ቋንቋ የተተረጎመ ቅጂ አብረው መላክ አለቦት ። ከ ትርጉሙ ጋራ የተረጎመው ሰው ሁለቱንም ቋንቋዎች እችላለሁ ብሎ የጻፈውን ማረጋገጫ ወረቀትም አብረው መላክ አለቦት ።
ባለቤትዎን ለማምጣት ከፈለጉ፡
- የጋብቻችሁን የምስክር ወረቀት ቅጂ ይጨምሩ።
- በፊት ያገቡ ከነበሩ፤ ያለፈው ጋብቻዎ መጠናቀቁን የሚያሳይ የሰነድ ቅጂ ያስገቡ ( አብዛኛውን ግዜ እነዚህ የፍቺ ወይም የሞት የምስክር ወረቀቶች ናቸው)።
- ይህ የተደረገው ጋብቻ በውሸት ለኢሚግሬሽን የተደረገ ጋብቻ ሳይሆን በሃቅ የተደረገ ጋብቻ እንደሆነ የሚያሳይ ማረጋገጫ ይላኩ። እንደ ምሳሌ የሚሆኑ፤
- እርሶና ባለቤትዎ ወላጆቻችቸው መሆናችሁን የሚያሳይ የልጆቻችሁ የልደት የምስክር ወረቀት
- የሁለታችሁ ስም ያለበት የባንክ ሂሳብ ወረቀት
- ምናልባትም ቤት የተክራያችሁበት የሁለታችሁ ስም ያለበት ውል
- እርሶንና ባለቤትዎን እንዲሁም ጋብቻችሁን በደንብ ከሚያውቁ ሰዎች የተጻፉ ደብዳቤዎች። እነዚህ ሰዎች የአሜሪካ ዜጎች መሆን የለባቸውም።
- በሚጽፉት ደብዳቤ ሙሉ ስማቸውን፣ አድራሻቸውን እና የተወለዱበት ዕለትና ቦታ መጨመር አለባቸው።
- እነኚህ ደብዳቤ የሚጽፉ ሰዎች ስለዝምድናችሁ በደንብ ማወቅ አለባቸው ለምሳሌ ለሰርጋችሁ በተደረገ ግብዣ ከነበሩ ወይም ከእናንተ ከሁለታችሁ ጋር ረዝም ያለ ግዜ ካሳለፉ መግለጽ አለባቸው።
- የሚቻል ከሆነ ደግሞ የሚልኩትን ደብዳቤ ወደ እርሶ ከመላካቸው በፊት ደብዳቤው በመንግስት ህጋዊ ተወካይ መፈረምና ማህተም በላዩ ላይ የታተመታበት መሆን አለበት።
ልጆን ማምጣት ከፈለጉ፡
- እናት ከሆኑ፤ ስምዎና የልጅዎ ስም ያለበት የልደት የምስክር ወረቀት ቅጂ ይላኩ።
- አባት ከሆኑ፤ የእርሶ እና የእናቲቱ ስም ያለበት የልጁ የልደት የምስክር ወረቀት፤ በተጨማሪም ልጁ ከመወለዱ በፊት ወይም ልጁ 18 ዓመት ከመሙላቱ በፊት ከእናቲቱ ጋር ባልና ሚስት እንደነበራችሁ የሚያሳይ የጋብቻ የምስክር ወረቀት ይላኩ። ያልተጋባችሁ ከሆነ ዝምድናችሁን እንዴት ማረጋገጥ እንደሚቻል የሚጠቁም ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ (USCIS) I-130 መምርያዎችን ይመልከቱ።
እህት ወይም ወንድሞን ማምጣት ከፈለጉ፡
- ቢያንስ አንድ የጋራ ወላጅ እንዳላችሁ የሚያሳይ የሁለታችሁን የልደት የምስክር ወረቀቶች ቅጂ ይላኩ።
- ሁለት የተለያዩ እናቶች ካላችሁ አባታችሁ ግን አንድ ከሆነ፤ አባታችሁ ሁለቱን እናቶች ወይም ከሁለቱ እናቶች ቢያንስ አንዱዋን እናት ያገቡበትን የጋብቻ የምስክር ወረቀት ቅጂ ይላኩ። አባትዬው ከእናቶቹ አንዷን ከፈቱ፤ የተፋቱበትን የፍቺ ምስክር ወረቀት ይላኩ። አባትዎ ማንኛዋንም እናት ያላገቡ ከሆነ፤ ዝምድናችሁን እንዴት ማረጋገጥ እንደሚቻል የሚጠቁም ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ (USCIS) I-130 መምርያዎችን ይመልከቱ።
እናትዎን ማምጣት ከፈለጉ፡
- የእናትዎ ስም ያለበት የራስዎን የልደት ምስክር ወረቀት ይላኩ።
አባትዎን ማምጣት ከፈለጉ፡
- የሁለቱ ወላጆችዎን ስም የሚያሳይ የራስዎን የልደት የምስክር ወረቀት ይላኩ።
- በተጨማሪም እናትና አባትዎ መጋባታቸውን የሚያሳይ የጋብቻ የምስክር ወረቀት ይላኩ። ወላጆችዎ ያልተጋቡ ከነበር፤ ዝምድናችሁን እንዴት ማረጋገጥ እንደሚቻል የሚጠቁም ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ (USCIS) I-130 መምርያዎችን ይመልከቱ።
የእንጀራ አባትዎን ወይም የእንጀራ እናትዎን ማምጣት ከፈለጉ፡
- የራስዎን የልደት የምስክር ወረቀት ይላኩ
- በተጨማሪም ወላጆችዎ ከእንጀራ እናትዎ ወይም ከእንጀራ አባትዎ ጋር የተጋቡበት የጋብቻ የምስክር ወረቀት ይላኩ። የተጋቡት እርስዎ 18 ዓመት ሳይሞላዎት በፊት መሆን አለበት።
- በተጨማሪም ሁለቱ ወይም አንዱ ከአሁን ቀደም አግብተው የነበሩና የተፋቱ መሆናቸውን የሚገልጹ ዶኩመንቶችን ይላኩ፡ ይህ በአብዛኛው የፍቺ ወይም የሞት የምስክር ወረቀት ይባላል።
አሳዳጊ ወላጆን ለማምጣት ከፈለጉ፡
- አሳዳጊ ወላጆችዎ እርሶን ለማሳደግ የቻሉት በህጋዊ መንገድ መሆኑን የሚያሳይ ዶኩመንት
- ሊያሳዱግዎት ከወሰድዎት በኋላ ወይም ከዛ በፊት ቢያንስ ለ2 ዓመታት ከ አሳዳጊ ወላጆችዎ ጋር መቀመጦን የሚያሳይ ዶኩመንት ይላኩ።
የሚፈለገው ዶኩመንት ከሌለኝስ?
የሚያስፈልጎት ዶኩመንቶች ከሌሎት፤ ማድረግ የሚችሉት ሌሎች ጥቂት አማራጮች አሉ፡
- እነኚህ ዶኩመንቶች ከሌሎት፤ እነሱን ለማግኘት መሞከር አለቦት። ለምሳሌ፤ ወደ ኤምባሲ ሂደው ቅጂ እንዲሰጦት መሞከር፣ የቤተሰቦን ወይም የጓደኞችዎን እርዳታ መጠየቅ።
- ከተጠየቀው ዶኩመንት ሌላ ተቀባይነት የሚኖረው ሌላ ዶኩመንት እንዳለ ማጣራት። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ክፍል (US Department of State) በዚህ ዌብሳይት ላይ ሊኖሩ የሚችሉ የሌሎች አማራጮች ዝርዝር አለው።
- የተጠየቁትን ዶኩመንቶች እንዳላገኙ የሚገልጽ ከመንግስት ጽህፈት ቤት ወይም ከኤምባሲ ደብዳቤ ያስጽፉ። እንደሚከተሉት የመሳሰሉ ሌሎች ዶኩመንቶችንም ለማግኘት መሞከር አለቦት፡
- የሃይማኖት መዝገብ፡ ከሃይማኖት ድርጅቶች እንደ ቤተክርስትያን፣ መስጊድ፣ የጸሎት ቤቶች ወይም ሲናጎግ ( synagogue) ከመሳሰሉ ቅጂ ለማግኘት ይሞክሩ። ይህም እርሶ በተወለዱ በሁለት ወራት ውስጥ ለእርሶ ጥምቀት የመሰለ ሃይማኖታዊ ተግባር ተፈጽሞ እንደነበር የሚያሳይ መሆን አለበት። ይህም ቀንና ሃይማኖታዊው ጉዳይ የተፈጸመበት የቦታ ስም፤ የተፈጸመው ምን እንደሆነና የወላጆቹን ስም የሚጠቅስ መረጃ ያለው መሆን አለበት ።
- የትምህርት ቤት መዝገብ፡ ትምህርት ቤት ከመሰለ የትምህርት ተቋም የተጻፈ ደብዳቤ። ደብዳቤውም ልጁ ትምህርት የጀመረበት ቀን፣ የልጁ የልደት የምስክር ወረቀት ወይም ትምህርት ሲጀምር ዕድሜው ምን ያህል እንደነበር፣ የተወለደበት ቦታ ና የወላጆቹ ስም የያዘ መሆን አለበት።
- የህዝብ ቆጠራ መዝገብ፡ የተመዘገበውን ሰው ስም፣ የተወለደበት ቦታና ዕለት ወይም ዕድሜ የያዘ የመንግስት መዝገብ።
- እርሶ ሊያረጋግጡት የሚፈልጉት ጉዳይ ሲካሄድ በወቅቱ ወይም በዝግጅቱ ከነበሩ ከአንድ ወይም ከዛ የሚበዙ ሰዎች ስለጉዳዩ ደብዳቤ እንዲጽፉ ጠይቋቸው፡
- እነኚህ ሰዎችም ስለጉዳዩ “የግላቸው የሆነ እውቀት” ሊኖራቸው ይገባል። ለምሳሌ በወላጆችዎ የሰርግ ግብዣ ላይ የነበሩ አጎትዎ ወይም እርሶ ሲወለዱ አዋላጅ ወይም አጋዥ የነበሩ ሴት ወይም ከባለትዳርዎ ጋር ስላሎት ግንኙነት በደንብ አድረጎ የሚያውቅ ጥሩ ጓደኛ ሊሆኑ ይችላሉ።
- ደብዳቤዎቹን የሚጽፉት ሰዎች የግድ የአሜሪካን ዜጋ መሆን የለባቸውም።
- እነኚህ ደብዳቤውን የሚጽፉ አንድና ሁለት ሰዎች በደብዳቤው ላይ ሙሉ ስማቸውን፣ አድራሻቸውን፣ የተወለዱበት ቀንና ቦታ፣ ስለጉዳዩ ምን እንደሚያውቁ እና ይህንን ደግሞ ሊያውቁ እንዴት እንደቻሉ መጻፍ አለባቸው።
- ከተቻለ ደብዳቤዎቹን ወደ እርሶ ከመላካቸው በፊት በመንግስት በተወከለ ሰው ማስፈርምና ማህተም ማስመታት አለባቸው።
ይህንን የI-130 ፎርም እና ዶኩመንቶቹን ወዴት ነው የምልከው?
የሚላክበት ቦታ በሚኖሩበት ቦታ የተወሰነ ነው። የ I-130 ፎርሞን የት እንድሚልኩ ለማጣራት እዚህ ዌብሳይት ላይ ይመልከቱ፤ በኦንላይንም መላክ ይችላሉ። በኦንላይን ስለሚደረግ የፎርም ማስገባት መመርያዎች እዚህ ይመልከቱ።
ይህንን የ I-130 ፎርም እና አጋዥ ዶኩመንቶችን ከመላኮ በፊት የሁሉንም ቅጂ አድረገው በራስዎ መዝገብ ላይ ይያዙ። ምንም እንኳን የዶኩመንቶቹ ኦሪጂናል ቢኖሮትም፣ በመጨረሻ አንድ ላይ በጠቅላላ ያስገቡት ፎርምና ዶኩመንቶች ቅጂ ማድረግ ያስፈልጎታል፤ ወደፊት ሊያስፈልጎት ይችላልና።
የ I-130 ፎርም ሞልቼ ካስገባሁ በኋላ ቀጥሎ የሚሆነው ምንድነው?
የI-130 ፎርሙን ሞልተው እስከነ አጋዥ ዶኩመንቶቹ እና ክፍሊቱ ወደ ዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ (USCIS) ይላኩ። ይህንን ካደረጉ በኋላ ዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ (USCIS) ለእርሶ፣ ለጥያቄ አቅራቢው (petitioner) ማሳሰብያዎችንና ደብዳቤዎችን በፖስታ ይልክሎታል። አንዳንዴ በኢሜልም ሊልኩ ይችላሉ፤ የሚላክሎትን ደብዳቤ በሙሉ ማቀብ አስፈላጊ ነው።
በቅድሚያ ዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ (USCIS) “I-797 የእርምጃ ማስታወቅያ” (I-797,Notice of Action) የሚባል ይልኩሎታል። ይህም ደብዳቤ እርሶ የላኩት የ I-130 ፎርም እንደደረሳቸው ይገልጻል። ይህ ደብዳቤ አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም፡
- የትኛው የ ዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ (USCIS) የአገልግሎት ማእከል በ እርሶ I-130 ጉዳይ ላይ እንደሚሰራ ይገልጻል። ይህ የ ዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ (USCIS) ዌብሳይት የ ዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ (USCIS)ን የግዜ ሰሌዳዎችንም ይሰጣል።
- ለጉዳዮ የደረሰኝ ቁጥር ይሰጦታል። ይህ ቁጥር EAC፣ WAC፣ LIN፣ SRC፣ NBC፣ MSC ወይም IOE የመሳሰሉ ሶስት ፊደሎች አሉት። ከእነዚህ ፊደሎች በኋላ 10 ቁጥሮች አሉ። ይህንን ቁጥር ለሚከተሉት መጠቀም ይችላሉ።
- ለጉዳዮ የቅድሚያ ቀን (priority date) ይሰጦታል። ይህ አስፈላጊ ነው ምክንያቱም ለዘመዶ ቪዛ መቼ እንደሚገኝ ይነግሮታል። በዚህ የውጭ ጉዳይ ክፍል ዌብሳይት (Department of State ዌብሳይት)፤ የመጨረሻውን ቪዛ ቡሊቲን (Visa Bulletin) በመጫን የሚጠበቀው ግዜ ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ ይችላሉ።
አንዳንዴ ዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ (USCIS) ለእርሶ ለጥያቄ አቅራቢው (petitioner) ተጨማሪ ዶኩመንቶች ያስፈልጉናል ብሎ ደብዳቤ ሊልክሎት ይችላል። ይህም ማረጋገጫ ለማግኘት የሚቀርብ ጥያቄ (Request for Evidence (አር ኤፍ ኢ RFE”) በመባል ይታወቃል። ይሄው አር ኤፍ ኢ (RFE) ምን ዓይነት ዶኩመንት ዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ (USCIS) ከእርሶ እንደሚፈልግና ይህንን ዶኩመንት የሚልኩበት የመጨረሻ ቀን ይነግሮታል። አብዛኛውን ግዜ የሚሰጦት ቀናት ከ90 እስከ 120 ቀናት ነው። ዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ (USCIS) በተጨማሪ የዲ ኤን ኤ (DNA) ምርመራ እንድታደርጉ ሃሳብ ሊያቀርብሎት ይችላል። ይህ የደም ምርመራ እርሶና ሊያመጡት ያሰቡት ተጠቃሚው ሰው (beneficiary) የምታደርጉት ምርመራ ነው። ምርመራውም እርሶና ተጠቃሚው ሰው እንደምትዛመዱ ማረጋገጥ ይችላል። ምርመራው በተወሰኑ ልዩ ላቦራቶሪ ውስጥ ነው የሚደረገው። ወደዚህ ዌብሳይት በመግባት የዲ ኤን ኤ (DNA) ላቦራተሪዎችን ዝርዝር ማግኘት ይችላሉ።
I-130 እንዲቀላጠፍ ማድረግ ይቻላልን?
አዎን። ዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ (USCIS) የ I-130 ማመልከቻዎ እንደደረሰው የሚገልጽ ደረሰኝ ካገኙ በኋላ፤ የ I-130 ጉዳዮ (ውሳኔ) እንዲቀላጠፍሎት መጠየቅ ይችላሉ።
የተቀላጠፈ ሂደት የማገኝ መሆኔን እንዴት ነው የማውቀው?
ጉዳዮ እንዲቀላጠፍ ከእነዚህ ከታች ከሰፈሩት ምክንያቶች በአንዱ ምክንያት ውስጥ በማለፍ ላይ ያሉ መሆን አለቦት፤
- አደጋኛ የሆኑ ሁኔታዎችና አስቸኳይ ህዝባዊ ምክንያቶች
- በተቋም ላይ ወይ በሰው ላይ የደረሰ ከፍተኛ የገንዘብ ኪሳራ
- ጥያቄ አቅራቢው ወይም ተጠቃሚው ሰው የሚከተሉትን በሚፈልገው መልኩ ካላደረጉ፤ እነኚህ ምክንያቶች ተቀባይነት አይኖራቸውም፡
- ጠቀሜታ ለማግኘት ወይም ጉዳዩ እንዲቀላጠፍ የሚያቀርቡትን ጥያቄ ምክንያታዊ በሆነ የግዜ ገደብ ውስጥ ሳያስገቡ ሲቀሩ ወይም
- ተጨማሪ ማረጋገጫ እንዲያቀርቡ ለተጠየቁት ጥያቄ በተጠይቀው የግዜ ገደብ መልስ ሳይሰጡ ሲቀሩ
- ጥያቄ አቅራቢው ወይም ተጠቃሚው ሰው የሚከተሉትን በሚፈልገው መልኩ ካላደረጉ፤ እነኚህ ምክንያቶች ተቀባይነት አይኖራቸውም፡
- ዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ (USCIS) ግልጽ የሆነ ስህተት ሲፈጽም
- በአሜሪካ መንግስት ጥቅም አንጻር ከፍተኛ ምክንያት ሲፈጠር (በመከላከያ ክፍሉ በዲ ኤች ኤስ ( Department of Defense of DHS) የአገር ደህንነትን የሚነካ አስቸኳይ ነገር ወይም አደገኛ ነገር ከተፈጸመ
ሂደቱ እንዲቀላጠፍ እንዴት ነው የምጠይቀው?
ጉዳዮ እንዲቀላጠፍሎ የሚከተሉትን ማድረግ ይችላሉ፤
- ወደ ዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ (USCIS) የግንኙነት ክፍል በስልክ ቁጥር 1-800-375-5283 መደወል ወይም
- በuscis.gov.በሚገኘውን የዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ (USCIS) ዌብሳይትውስጥ ያለውን ‘ኤማን ይጠይቋት” ወይም “Ask Emma” የሚል የውይይት ገጽ በመክፈት ይጠይቁ። ይህንን ለማኘት በገጹ ከወደ ላይና በቀኝ ያለውን “Ask Emma” ምልክት በመጫን ያገኙታል።
- ጥይቄዎን ለማጠናቀቅ፤ የደረሰኝ ቁጥር ሊኖሮት ይገባል። ዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ (USCIS) ይህ የደረሰኝ ቁጥር ከሌለው የአገልግሎት ጥያቄ ሊልክ አይችልም። ይህ የደረሰኝ ቁጥር ዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ (USCIS) የላኩልን ማመልከቻ ደርሶናል ብለው በላኩሎት በ I-797C ዶኩመንት ውስጥ ይገኛል።
ጉዳዮ እንዲቀላጠፍሎት በመጠየቅ ከ ዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ (USCIS) ወኪል ጋር ከተደዋወሉ ወይም ከተወያዩ በኋላ፤ የዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ (USCIS) የግንኙነት ማእከል ጥያቄዎን ወደ ሚመለከተው መስርያ ቤት ይልካል። ከስልኩ ግንኙነት በኋላ፤ ይህ መስርያ ቤት ምናልባት ተጨማሪ መረጃ ወይም ተጨማሪ ዶኩመንት የሚያስፈልገው ከሆነ እንድትልኩ ወይም እንድታቀርቡ ሊጠይቆት ይችላል። ይህንን ጥያቄ የሚያቀርብሎት በስልክ ወይም በኢሜል ሊሆን ይችላል።
ጉዳዮ እንዲፋጠን የሚሰጠው ውሳኔ መጀመርያ ላይ ባቀረብኩት ጥያቄ ላይ ተጽእኖ ሊያደርግ ይችላልን?
ጉዳይ እንዲፋጠን የሚሰጠው ውሳኔ መጀመርያ ያቀረቡት ጥያቄ ውድቅ እንዲሆን ወይም እንዲፈቀድ በማድረግ ላይ ተጽእኖ አያደርግም።
ጥያቄዎ እንዲፋጠን የጠየቁት ጥያቄ አንዴ በአዎንታ መልስ ሲያገኝ፤ ከዛ በኋላ ዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ (USCIS) ከአዘቦቱ ቀን በተፋጠነ መልኩ ውሳኔውን ተፋጥኖ ይሰጣል። የቀረቡት ጥያቄዎች ሁሉ የሚታዩት አንድ በአንድ ሲሆን ዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ (USCIS) ጉዳዮች እንዲፋጠኑ መፍቀድ ወይም መከልከል ይችላል።
ለተጨማሪ መረጃ፤ ይህንን ይመልከቱ ዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ (USCIS) የፖሊሲ መጽሄት፣ ቮሉም 1፣ ክፍል A፣ ህዝባዊ አገልግሎት፣ ምዕራፍ 5፣ ጉዳዮችን ለማፋጠን የሚቀርብ ጥያቄ።
ጉዳዬን በተመለከተ አንድ ትክክል ያልሆነ ነገር ተፈጽሟል የሚል አስተሳሰብ ቢኖረኝስ?
አስፈላጊ፡ ከሚያዝያ (April) 2025 ጀምሮ የኡምባድስማን (Ombudsman) ጽህፈት ቤት ስራውን አቁሟል የሚል ሪፖርት አለ። ይህም የኡምባድስማን (Ombudsman) ጽህፈት ቤት የቀረቡለትን ጥያቄዎች በአሁኑ ወቅት አይመለከትም ያለው ማለት ነው። መንግስት ስለዚህ ለውጥ በይፋ ያወጣው ምንም ነገር የለም። ጥያቄዎችን የማቅረብ መስመር ግን አሁንም ለኦምባድስማን መስርያ ቤት ክፍት ነው ያለው። አሁንም ጥያቄዎችዎን ለኦምባድስማን መስርያ ቤት አቅርቡና መልስ ማግኘትዎንና አለማግኘቶን ለማወቅ ይሞክሩ። እኛ ግን በተጨማሪ የምንሰጠው ሃሳብ እርዳታ እንዲያደርግሎት በአሜሪካ ምክር ቤት ወይም ኮንግሬስ ውስጥ ያለውን ወኪሎን ለማግኘት እንዲሞክሩ ነው። አሁንም የኦምባድስማን (Ombudsman) ጽህፈት ቤትን ለማግኘት የሚመርጡ ከሆነ፣ ከወደታች አንዳንድ አስፈላጊ መረጃዎች ሰፍረዋል።
የኦምባድስማን (Ombudsman) የዜግነትና የኢሚግሬሽን አገልግሎት ጽህፈት ቤት፤ ሰዎች ከዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ (USCIS) ጋር ችግር ሲያጋጥማቸው ችግሩን ለመፍታት ያግዛል። የኦምባድስማን ጽህፈት ቤት የዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ (USCIS) አካል ስላልሆነ ጉዳዮችን መቀበልና መከልከል አይችልም። ይሁንና ከዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ (USCIS) ጋር በመገናኘት ከሚከተሉት ውስጥ አንዱ ካጋጠሞት ሊያግዝ ይችላል፡
- ከ ዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ (USCIS) ደብዳቤ ወይም የተሰጠ ውሳኔ ሳይደርሶት ዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ (USCIS) ግን ልከንሎታል ሲል
- ተጠቃሚው ሰው (beneficiary) ብቁ ከሚያደርገው “የዕድሜ ክልል ሊወጣ” ትንሽ ግዜያት ሲቀረው (ይህም በአብዛኛው አንድ ልጅ ዕድሜው 21 ዓመት ሊደርስ ይቀርብና በወላጆቹ ማመልከቻ ውስጥ መቆየት ሳይችል ሲቀር ማለት ነው)
- በዶኩመንቶችዎ ውስጥ ስህተት ሲኖር
- ለጉዳዮ ሂደት ከተሰጠው የ60 ቀናት ግዜ ዘግይተው ሲያስረክቡ
- የጠፉ ፋይሎች ሲኖሩ ወይም ፋይሎን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በማስተላለፍ ረገድ ችግር ሲፈጠር
- ዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ (USCIS) ከባድ ስህተት ፈጽሟል የሚል አስተሳሰብ ሲኖሮት
እርዳታ ለማግኘት፤ በኦንላይን የጉዳይ ድጋፍ ጥያቄ ማቅረብ ይችላሉ። በተጨማሪም እዚህ የሚገኘውን ፎርም ከኦንላይን አውርደው በኢሜል ወደ cisombudsman@hq.dhs.gov. ይላኩ። አንዳንዴ ፎርሙን ለመክፈት Microsoft’s Internet Explorer browser መጠቀም ይቀላል። ከ5 ሜጋባይት የሚተልቁ አባሪዎችን (attachments) አትላኩ። ለተጨማሪ ዝርዝር መመሪያዎች የኡምባድስማን ጽህፈት ቤት ዌብሳይትን እዚህ ይመልከቱ።
በከፍተኛው ምክር ቤት (ኮንግሬስ) ያለውን ወኪሎንም እርዳታ እንዲያደርግሎት መጠየቅ ይችላሉ። ከኮንግሬስ ወኪሎ እርዳታ ለመጠየቅ እንዴት እንደምትችሉ የሚያስረዳ የኢራፕ (IRAP) መመርያ እዚህ ያገኛል።
ያስገባሁት I-130 ተቀባይነት ካገኘ በኋላ የሚቀጥለው ነገር ምንድነው?
በዚህ በቤተሰብ ላይ የተመረኮዘ የኢሚግሬሽን ሂደት፤ ተቀባይነት ያገኘ የ I-130 ማመልከቻ ነው የመጀመርያ እርምጃ። ይህ መመርያ በዚህ የመጀመርያ እርምጃ ላይ የተወሰነና ያተኮረ ነው። ከዚህ በኋላ ያለው የተቀረው ሂደት ለመከናወን የሚፈጀው ግዜ በቤተሰብ ዝምድና ዓይነት ላይ የተመረኮዘ ነው።
ለአንዳንድ ዘመዶች ቪዛ ወድያውኑ ሊገኝ ይችላል። በመሆኑም እነኚህ ቪዛ ያገኙ ሰዎች የI-130 ማመልከቻቸው ተቀባይነት እንዳገኘ ወድያውኑ ቪዛ የማግኘት ማመልከቻ ማስገባት ይችላሉ። ለሌሎች ዘመዶች ግን በየዓመቱ የተወሰኑ ቪዛዎች ብቻ ስላሉ፤ ዘመዶች የቪዛ ማመልከቻ ሂደቱን ከመጀመራቸው በፊት ብዙ ግዜ፣ አንዳንዴም ዓመታት ሊጠብቁ ይችላሉ። ቪዛ ለማግኘት ስለሚወስደው ግዜ ተጨማሪ መረጃ ከፈልጉ መረጃ በ ስቴት ዲፓርትመንት የቪዛ መጽሄት (State Department’s visa bulletin) ላይ ማግኘት ይችላሉ።
ቪዛ ሲገኝ፤ የሚወስዱት የሚቀጠለው እርምጃ ዘመዶ በሚኖርበት ቦታ ይወሰናል። ዘመዶ አሜሪካን አገር ውስጥ ከሆነ ያለው፤ ወድያውኑ ያለውን የመኖርያ ፈቃድ ወደ ህጋዊና ቋሚ የመኖርያ ፈቃድ ሊያስተካክል ይችል ይሆናል። የመኖርያ ፍቃድን ወደ ህጋዊና ቋሚ የመኖርያ ፈቃድ ስለማስተካከል ያለው መረጃ በዩ ኤስ ሲ አይ ኤስ ዌብሳይት ውስጥ ይገኛል። ዘመዶ የሚገኛው ከአሜሪካን አገር ውጪ ከሆነ፤ ወደ አሜሪካን አገር እንደ አንድ ህጋዊ ተቀማጭ ለመግባት፤ የስደተኛ ቪዛ ለማግኘት ማመልከቻ ማስገባት አለበት። ስለዚህ የስደተኛ ቪዛ ለማግኘት መደረግ ስላለበት ማመልከቻ ተጨማሪ መረጃ ከመንግስት የስቴት ዲፓርትመንት ዌብሳይት ማግኘት ይቻላል።
የአለም አቀፍ የስደተኞች እርዳታ ፕሮጀክት (IRAP) ለአንዳንድ ስደተኞች እና ተፈናቃዮች ነፃ የህግ እርዳታ ይሰጣል።
- IRAP አንዳንድ ሰዎች አገልግሎት እንዲያገኙ እና የስደተኛ እና የቪዛ ማመልከቻዎችን እንዲያዘጋጁ ይረዳቸዋል።
- IRAP የየትኛውም መንግስት፣ IOM ወይም UNHCR አካል አይደለም።
- IRAP የስደተኛ ደረጃ ወይም ቪዛ ሊሰጥ ወይም ጉዳዮችን ማፋጠን አይችልም።
- IRAP የገንዘብ ድጋፍ መስጠት፣ መኖሪያ ቤት ማግኘት ወይም መክፈል፣ ወይም ሥራ ማግኘት አይችልም።
- ሁሉም የ IRAP እርዳታ ነፃ ነው። ማንም ሰው ከIRAP ጋር ግንኙነት ያለው ገንዘብ ወይም ሌላ አገልግሎት ሊጠይቅዎት መብት የለውም።
IRAP ሰዎችን በፍላጎታቸው እና ለስደት ሁኔታ ብቁነታቸውን መሰረት አድርጎ ለመርዳት ይወስናል። IRAP በማንኛውም ሌላ ማህበራዊ ወይም ፖለቲካዊ ወይም ሃይማኖታዊ መመዘኛዎች ሰዎችን ለመርዳት አይወስንም።
ይህ ድህረ ገጽ ለአንዳንድ ስደተኞች ስለሚገኙ የህግ ሂደቶች አጠቃላይ መረጃ ይሰጣል። ለግል ማመልከቻዎች እንደ ህጋዊ ምክር አይደለም።
መስፈርቶች ሊለወጡ ይችላሉ። ጥያቄዎን ሲወስኑ ሁል ጊዜ ከመንግስት ወይም ከኤጀንሲው ወቅታዊ መስፈርቶችን ያረጋግጡ።
በስደተኞች ድንገተኛ አደጋ ውስጥ ከሆኑ፣ በሚኖሩበት አገር ያለውን የ UNHCR ቢሮ እንዲያነጋግሩ እንመክራለን።
Comments
0 comments
Please sign in to leave a comment.